image
image
image
image
image

የሰላም ሠራዊትን ማጠናከር አስፈላጊ መኾኑን ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገለጹ።

ሀምሌ 4, 2017
የአዲስ አበባ ከተማ አሥተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ በ3ኛው የአዲስ አበባ ምክር ቤት 4ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 4ኛ መደበኛ ጉባኤ ላይ የምክር ቤት አባላት ላነሷቸው ጥያቄዎች ምላሽ እና ማብራሪያ ሰጥተዋል። ከንቲባ አዳነች አቤቤ በምላሻቸው የሰላም እና ደኅንነት ሥራዎች አበረታች መኾናቸውን ገልጸዋል። አሁንም የዝርፊያ እና የጸረ ሰላም ኀይሎች እንቅስቃሴ እንዳለ ተናግረዋል። ሕዝቡ የሰላሙ ዋነኛ ባለቤት በመኾኑ የሰላም ሠራዊቱን በቁጥር፣ በጥራት እና በብቃትም ማጠናከር አስፈላጊ መኾኑን አስገንዝበዋል። ከተማዋ የወንጀለኞች መሸሸጊያ እንዳትኾን ዘመናዊ የሴኩሪቲ መሳሪያዎች መትከል እና በሕዝብ እና በጸጥታ ኀይሎች መካከል ያለውን ቅንጅት ማሳደግ ትኩረት እንደተሰጠው አንስተዋል። በተሠራው ሥራ ከፍተኛ ውጤት እንደተመዘገበበት አብራርተዋል። ይህ ጥረት ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም አመላክተዋል። የመሬት ልማት አሥተዳደር አገልግሎቶችን ፈጣን እና ተደራሽ ለማድረግ የተጀመሩ የዲጂታል አገልግሎት ሥራዎች በጥሩ ሁኔታ ላይ መኾናቸውንም ጠቁመዋል። አሁን ባለው ደረጃ 347 አገልግሎቶችን በ"መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት" ለማስጀመር ቅድመ ዝግጅት መጠናቀቁን ገልጸዋል። በቀጣይም የዕውቀት እና ልምድ ልውውጥን በማስፋት ዲጂታል አገልግሎቱን ለማሻሻል እንደሚሠራ ነው ያስገነዘቡት። ከ4ሺህ በላይ መሪዎች፣ ባለሙያዎች እና ደላሎች በሌብነት እና በሙስና ወንጀል ተሰማርተው በመገኘታቸው ሕግ የማስከበር ተግባር መፈጸሙን ተናግረዋል። ይህም ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ከንቲባዋ አስታውቀዋል። አገልጋይ ማገልገል ግዴታው፣ ተገልጋይም መገልገል መብቱ በመኾኑ ሙስናን መዋጋት ተገቢ እንደኾነም አጽንኦት ሰጥተዋል። የነዋሪዎችን የቤት ጥያቄ ለመመለስ በተሠራው ሥራ ከ55 ሺህ በላይ ነዋሪዎችን የቤት ባለቤት እንዳደረጉ ከንቲባዋ ገልጸዋል። በቀጣይ በጀት ዓመት የቤት ግንባታ በልዩ ትኩረት እንደሚሠራ እና መንግሥት ብቻውን መመለስ ስለማይችል ባለሃብቶችን በመሬት አቅርቦት እና ድጋፍ በመስጠት በቅንጅት እንደሚሠራ አስታውቀዋል። የኑሮ ውድነትን ለመግታት እና ሰው ሠራሽ የዋጋ ንረትን ለመከላከል የከተማ አሥተዳደሩ በድጎማ፣ በኅብረት ሥራ ማኅበራት፣ በገበያ ማዕከላት እና በእሑድ ገበያ በተመጣጣኝ ዋጋ ምርቶችን በማቅረብ፣ በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ ባሉ የኅብረተሰብ ክፍሎች ላይ የኑሮ ጫና እንዳይበረታ እየተሠራ መኾኑን ገልጸዋል። ይህ ተግባርም ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ነው ያስገነዘቡት። ጉባኤው በከሰዓት ውሎው የ2017 በጀት ዓመት የኦዲት ሪፖርት ቀርቦለት ውይይት አድርጎበታል። በነገ ውሎው ደግሞ የዳኞችን፣ የተለያዩ ሹመቶችን እና በአዲስ የሚቋቋሙ ተቋማትን በአዋጅ እንደሚያጸድቅ ይጠበቃል። ዘጋቢ፦ አዲሱ ዳዊት የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ

መልዕክትዎን ይላኩ