የሰላምና ጸጥታ አስተዳደር ቢሮ ስልጣንና ተግባር
- የደንብ ማስከበር ባለሥልጣንን በበላይነት ይመራል፤ ያስተባብራል፤
- የብሔራዊ የፀጥታና የሰላም ፖሊሲን መሠረት በማድረግ የከተማውን የአስተዳደርና ፀጥታ ጉዳይ ተጨባጭ ሁኔታ ያገናዘበ ከተማ አቀፍ ፖሊሲ ይቀርፃል፤ ስትራቴጂ ይነድፋል፤ ህግ ያመነጫል፤ ሲጸድቅም ተግባራዊ መሆኑን ይከታተላል፤ ያረጋግጣል፤
- በፀጥታ ጉዳዮች የከተማው አስተዳደር ዋና የፀጥታ አማካሪ ሆኖ ይሰራል፤ ለፀጥታና ሰላም አስጊ የሆኑ ጉዳዮች ላይ ተገቢ የሆነ አፋጣኝ እርምጃ ይወስዳል፤ አስፈላጊ ሆኖ ሲገኝም እንደ አግባብነቱ ራሱ ወይም ከሚመለከተው አካል ጋር በመቀናጀት የእርምት እርምጃ ይወስዳል ወይም እንዲወሰድ ያደርጋል፤
- የግጭት መንስዔዎችን በጥናት ይለያል፣ ግጭት እንዳይከሰት ይከላከላል፤ ሲከሰትም ባህላዊና ዘመናዊ የግጭት አፈታት ዘዴዎችን በመጠቀም ይፈታል፤
- በከተማው ልዩ ልዩ ሀይማኖትና ቤተ-እምነት ተከታዮች መካከል ሰላምና መከባበር እንዲሰፍን ለማድረግና ግጭትንም ለመከላከል እንዲቻል አግባብነት ካላቸዉ የፌደራልም ሆነ የከተማው አስተዳደር አካላት፣ የኃይማኖት ተቋማትና ከሌሎች ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመተባበር ይሠራል፤
- በግጭት መከላከል፣ አያያዝም ሆነ አፈታት፣ በነዋሪው ደህንነት፣ ሰላም እና ፀጥታ አጠባበቅ ጉዳዮች ዙሪያ አግባብነት ካላቸው የፌደራል፣ የክልል፣ የከተማ አስተዳደር እና ሌሎች አካላት ጋር የሥራ ግንኙነቶችን ያደርጋል፤ እንደአግባብነቱ ችግሮችን በተናጠል ወይም በጋራ ይፈታል፤
- ህግና ስርዓት መከበሩንና የህብረተሰቡ ሰላምና ደህንነት መጠበቁን ይከታተላል፣ ይቆጣጠራል፣
- ህገ-መንግስታዊ ስርዓቱን በኃይል ለማፍረስና በስውር የነዋሪውንና የመንግስትን ጥቅም ጉዳት ላይ ለመጣል የሚንቀሳቀሱ ግለሰቦችን፣ ቡድኖችንና ድርጅቶችን በመከታተል ነዋሪውንና ሌሎች የሚመለከታቸውን አካላት በማሳተፍ ይከላከላል፤ ይቆጣጠራል፤
- ከጸጥታ አስተዳደር ጋር የተያያዙ ቅሬታ እና አቤቱታዎችን ይቀበላል፤ ይመረምራል፤ እንዳግባብነቱ ራሱ ወይም በተጠሪ ተቋም ወይም በሌሎች በሚመለከታቸው አካላት ቅሬታዎቹና አቤቱታዎቹ መልስ እንዲያገኙ ያደርጋል፤ አፈጻጸሙን ይከታተላል፤
- በፌደራል መንግስት የተመዘገቡ እና ፈቃድና እድሳት የተሰጣቸውን የሀይማኖት ተቋማት እና የብዙሀን ማህበራት ለመረጃነት ይመዘግባል፤ መረጃ ያደራጃል፤ ህገ-መንግስቱንና ሌሎች ህጎችን አክብረው ስለመስራታቸው ይከታተላል፤ ይቆጣጠራል፤ እርምጃ እንዲወሰድ ያደርጋል፤ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ተቀናጅቶ ይሰራል፤
- ለህግ አስከባሪ አካላት እና ለነዋሪዎች በወቅታዊ ጉዳዩች ዙሪያ አቅማቸውን በመገንባት የህዝብ አገልጋይነት ሚናቸውን እንዲወጡ ያደርጋል፤
- የሌሎች ህጎች ድንጋጌዎችና አሰራሮች እንደተጠበቁ ሆነው የጦር መሳሪያ ፈቃድ በሚመለከት የትብብር ደብዳቤ ይሰጣል፤ መረጃ ያደራጃል፤ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በቅንጅት ይሰራል፤
- በከተማው የጦር መሣሪያ አጠቃቀምና አያያዝ በተመለከተ የምዝገባ አፈጻጸምን ይከታተላል፤
- የህብረተሰቡን ተሳትፎ በማጎልበት እና ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመቀናጀት ወንጀል፣ የደንብ መተላለፍ እና ተያያዥ ሕገ ወጥ ተግባራት እንዳይፈፀሙ የማስተባበር ስራዎችን ይሰራል፤ ተፈጽሞ ሲገኝ ህጋዊ እርምጃ እንዲወሰድ ያደርጋል፣
- የማህበረሰብ አቀፍ ፖሊስ አገልግሎት በህብረተሰብ ተሳትፎ ላይ እና በመስፈርቱ መሰረት ስለመከናወኑ ይከታተላል፤ ይቆጣጠራል፤ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በቅንጅት ይሰራል፤
- የፀጥታ አስተዳደር እና ሌሎች ተያያዥነት ያላቸው ጉዳዮች ላይ ለተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠናዎችን ይሰጣል ወይም እንዲሰጥ ያደርጋል፤
- የፀጥታ ሁኔታ መረጃ ይሰበስባል፣ ያደራጃል፣ ጥናትና ምርምር ያደርጋል፣ ውጤቱን ለሚመለከተው አካል ያቀርባል፤ በሚሰጠው ውሳኔ መሠረት ተግባር ላይ እንዲውል ያደርጋል፣ አፈጻጸሙንም ይከታተላል፤
- የመንግስትና የግል ተቋማትን እና ነዋሪውን በአካባቢያቸው የፀጥታ፣ ሰላም እና ተያያዥ ጉዳዮች ላይ የሚሳተፉበትን ስልት ይቀይሳል፤ ተቋማዊ አደረጃጀት ይፈጥራል፤ ያስተባብራል፤
- በከተማው ክልል ውስጥ የተፈጥሮና ሰው ሰራሽ አደጋዎች በሚያጋጥሙበት ወቅት ከሌሎች ባለደርሻ አካላት ጋር በመተባበር የጉዳቱ መጠን እንዳይባባስ አስፈላጊውን ሁሉ ያደርጋል፤ በአደጋው ክልል ውስጥ የሚገኙ ማህበረሰብ አካላት የህይወትና የንብረት ደህንነት እንዲጠበቅ ያደርጋል፤
- ስለሰላማዊ ሰልፍ፣ በአደባባይ ላይ ስለሚከናወኑ የተለያዩ ፕሮግራሞች እና ስብሰባዎች ከንቲባውን ያማክራል፤ አፈጻጸሙን ይከታተላል፤
- የመንግስትና የግል ተቋማት እንዲሁም የአካባቢ ቅጥር ጥበቃ በተመለከተ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በትብብር ይሰራል፤
- የሰላም እና የፀጥታ ምክር ቤት አደረጃጀትና አሰራር አጥንቶ ለከንቲባው ያቀርባል፤ ሲወሰንም ተግባራዊ ያደርጋል፡፡